Lema Regassa ለማ ረጋሳ
የአቶ ለማ ረጋሳ ቡኔ አጭር የህይወት ታሪክ
አቶ ለማ ረጋሳ ከእናታቸው ከወ/ሮ ጌጤ ማሞ እና ከአባታቸው አቶ ረጋሣ ቡኔ ሰኔ 5 ቀን
በ1940 ዓም በአርሲ ጠቅላይ ግዛት፣ በጭላሎ አውራጃ፣ በዶዶታ ወረዳ በአሁኑ አጠራር በሎዴ
ጦሣ ወረዳ በሁሩታ ከተማ ተወለዱ፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በዚያው በአርሲ
ጠቅላይ ግዛት በጭላሎ አውራጃ በዶዶታ ወረዳ፣ በሁሩታ ከተማ በንጉስ ኃይለመለኮት
የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉ ሲሆን የ2ኛ ደረጃ
ትምህርታቸውን በአሰላ ራስ ዳርጌ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተምረዋል፡፡
ቀድሞ በነበረው ስርዓተ ትምህርት መሰረት ለመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት መምህርነት ኮርስ
ተወዳድረው በማለፋቸው በ1963 ዓም ለሁለት ዓመት የሙያና የቀለም ትምህርት ጂማ
መምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ገብተው በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡
አቶ ለማ ረጋሣ ከጅማ መምህራን ማሰልጠኛ ከተመረቁ በኋላ ለሥራ ጎጃም ጠቅላይ ግዛት
በመመደብ በመተከል አውራጃ በተለያዩ ቦታዎችና በደብረማርቆስ ከተማ በመምህርነት
አገልግለዋል፡ በሥራ ዝውውርም ወደ ሸዋ ክፍለ አገረ በመምጣት በዝዋይ የህጻናት አምባና
በኋላም በሰበታ መርሃ እውራን ተቋም በመምህርነትና በሃላፊነት ሲሰሩ ቆያተዋል፡፡
በመቀጠልም በነበራቸው ብቃትና ታታሪነት በሥራ ዝውውር ትምህርት ሚኒስቴር በልዩ
ፍላጎት ትምህርት ክፍል በተለያዩ የሥራ ሃላፊነት ደረጃዎች ላይ በጡረታ ከመደበኛ
የመንግሥት ሥራ እስከተሰናበቱበት እስከየካቲት ወር 1999 ዓም ድረስ አገራቸውንና
ሕዝባቸውን በቅንነት አገልግለዋል፡፡
አቶ ለማ ረጋሣ በአጭሩ ሥራ ዘመናቸው፧
❖ ከ1964 – እስከ -1970 ዓ ም በመጀመሪያ ደረጃ መምህርነት፤
❖ ከ1970 -እስከ -1974 ዓ ም በደብረማርቆስ አውራጃ የትምህርት ማበልጸጊያ ማእከል
ቴክኒሽያንነት፧
❖ ከ1974 -እስከ 1980 ዓ ም በሰበታ መርሃ እውራን ት/ቤት ለዓይነ ስውራን
ተማሪዎች በብሬይል ክህሎት ትምህርት መምህርነት
❖ ከ1980 -እስከ 1981 ዓ ም በሸዋ ት/ቤቶች ጽ/ቤት የልዩ ፍላጎት ትምህርት
አስተባባሪነት፣
❖ ከ1981 – እስከ 1996 ዓ ም ድረስ በትምህርት ሚኒስቴር በመምህራን ስልጠና እና
በትምህርት ሥራ አመራር የመምህራን ልማት የልዩ ፍላጎት ትምህርት ዘርፍ
ከፍተኛ ኤክስፐርት ሆነው በመስራት፤
❖ ከመጋቢት 1996 -እስከ ግንቦት 1998 ዓ ም በከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራም
የምርምርና የፕሮጀክት ጥናት ተጠሪነት፤
❖ ከሰኔ 1997 -እስከ የካቲት 1999 ዓ ም በትምህርት ሚኒስቴር የትምህረት ጉዳዮች
ሃላፊ በመሆን በአጠቃላይ ለ 35 (ለሰላሳ አምስት) ዓመታት በትምህርት ሚኒስቴር
ልዩ ልዩ ዘርፍ ያገለገሉ አንጋፋ የትምህርት ባለሙያ ነበሩ፡፡
አቶ ለማ ረጋሳ ለትምህርት በነበራቸው ከፍተኛ ፈቅርና ችሎታ ከጅማ መምህራን ማሰልጠኛ
በአንደኛ ደረጃ ትምህርት መምህርነት ከተመረቁ በኋላ፤
● በፊንላንድ በዩቫስኩላ ዩኒቨርሲቲ ከ1977 -እስከ 1980 ዓም በዓይነ ሥውራን ትምህርት
መስክ በአድቫንስድ ዲፐሎማ እና በቢኤ ዲግሪ ተመርቀዋል፣ በመቀጠልም፤
●
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከ1990 1992 ዓ ም በልዩ ፍላጎትና አካቶ ትምህርት
በድህረ ምረቃ ፕሮግራም በኤም ኤ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡
የነበራቸውን የትምህረትና የሙያ እውቀት ለማሳደግ በፊንላንድ በኒሎማኬ ኢንስቲትዩት
በዩኖቫስኬላ ዩኒቨርሲቲ በክሊኒካል ኒውሮ-ሳይኮሎጂ ትምህርት መስክ የአድቫንስድ
ፕሮፌሽናል ዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡
.
–
አቶ ለማ ረጋሣ በኑሮ ዘመናቸው ባለትዳር፣ ቤተሰባቸውን ወዳድና የሁለት ሴትና የሁለት
ወንድ ልጆች እና የ-9 (የዘጠኝ) የልጅ ልጆች አባትና አያት ነበሩ፡፡
አቶ ለማ ረጋሣ በመኖሪያ አካባቢያቸውም ልዩ ልዩ የልማት ተግባራትን በማስተባበር፣
በማህበራዊ ኑሮ ዘርፍም ንቁ ተሳታፊና በእድር አመራርነት መልካም ምሳሌነት ያላቸው፣አመለ
ሸጋ፣ ተናግረው ሰው የማያስቀይሙ፣ ታጋሽና ጨዋ አባት ነበሩ፡፡
የጌታ ትእዛዝ “አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለv” በሚለው መሰረት ሆነና፣ አቶ ለማ ረጋሣ
ለአጭር ቀናት ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቢቆዩም ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ ም
ከሌሊቱ 8፡30 ሰዓት ከዚህ ዓለም በሥጋ ሞት ተለይተዋል፡
ለአቶ ለማ ረጋሣ ባለቤት፣ ልጆች፣ ወንድሞች፣ እህቶችና ዘመድ አዝማድ በሙሉ መጽናናትን
እየተመኘን ነፍሳቸውን በፃድቃን ጎራ እንዲያኖርልን ፈጣሪያችንን እንለምናለን፡፡
አሜን!!